“ቅርስ አላውቅም”
ፕራይቬታይዜሽን ኤጄንሲ የመንግስት
ድርጅቶችን ጨረታ በማውጣት ይሸጥ ነበር።
እስከ1993 ዓ.ም የቦርዱ ሰብሳቢና ስራ
አስኪያጅ አሰፋ አብርሃ፣ አባላት የጤና ጥበቃ
ሚ/ር ዶ/ር ከበደ ታደሰ፣ የጠ/ሚ/ር አማካሪ
መንግስቱ ለማ፣ የፍትህ ሚ/ር ማህተመ
ሰሎሞን…ከሰባቱ ይጠቀሳሉ። በጨረታ
ከቀረቡት ከ40 በላይ መንግስታዊ ተቋማት
አንዱ ጣይቱ ሆ/ል ነበር። ሶስት ጊዜ ጨረታ
ቢወጣም የሚገዛ ጠፋ። ዶ/ር ከበደ ለበርዱ
ሲናገሩ « ይህ ቅርስ ነው፤ ሊሸጥ
አይገባውም! አርበኞች ማህበርን አናግሬ
ያቀረቡት ቅሬታ ተመሳሳይ ነው። እኔ በዚህ
ላይ ገለልተኛ አቋም ነው ያለኝ» ይላሉ።
አሰፋ አብርሃ መለስ ዜናዊ ዘንድ ይገቡና «
በጣይቱ ሆቴል ውስጥ 500 ቅርሶች አሉ።
ይህን ጨምሮ ሆቴሉ ታሪካዊ ቅርስ በመሆኑ
መሸጥ የለበትም» በሚል ይናገራሉ። መለስ
ዜናዊ በቁጣ « እኔ ቅርስ አላውቅም፤
ባወጣው ዋጋ ሽጡት። አይ.ኤም.ኤፍ
የመንግስት ተቋማትን ካልሸጣችሁ የገንዘብ
እርዳታ አንለቅም..ብለውናል። ቅርስና ታሪክ
አትበሉኝ..» ሲሉ ተናገሩ። አቶ ፍፁም ለተባለ
ባለሃብት በ3ሚሊዮን ተሸጠ። ፍፁም
በኡጋንዳ ለረጅም አመት የኖረና
በኢንቨስተርነቱ በአገሪቱ ፕ/ት ጭምር
የሚደነቅ ሰው ነው። አገሬ ልስራ ብሎ ጓዙን
ጠቅልሎ መጣ። በተለያየ መስክ ተሰማራ።
ጣይቱንም ገዛ። ሲሸጥ በፊርማቸው
ያፀደቁት መለስ ዜናዊ ነበሩ። በኋላ እስር
ቤት የገቡት ምንም የማያውቁት ባለሃብቱና
አቶ አሰፋ ነበሩ። ቢሆንም የቦርድ አባላቶች
ፍ/ቤት ቀርበው በመለስ ዜናዊ የውሳኔ
ፊርማ መሸጡን ገለፁ። ፍፁምና አሰፋ
ከሰባት አመት እስር በኋላ ከዚህ ክስ ነፃ
ተባሉ። ፍጹም ከጣይቱ ጋር በተያያዘ በመቶ
ሚሊዮን የሚቆጠር የባንክ እዳ
እንዲጣልባቸው ተደረገ። አሳዛኝ በደል ነው
የተፈፀመባቸው። እነሆ ጣይቱ ትላንት
ተቃጠለ። መለስ በህይወት ቢኖሩ ምን ይሉ
ይሆን?

Comments