የማዕከላዊ ጭካኔ ያረፈባቸውን እማዋይሽ አለሙን እንወቃቸው


By: Dawit Solomon
ወይዘሮ እማዋይሽ አለሙ ደልደል ያለ ሰውነት፣አጠር ያለ ቁመና ያላቸው የፊት ገጽታቸው በብዙ ፈተና ውስጥ ለማለፋቸው እማኝነት የሚሰጥላቸው ፣ከአንደበታቸው የሚወጡ የተመጠኑና የተመረጡ ቃላት ከሚገኙበት የቃሊቲ ወህኒ ቤት በላይ ጮሆ የሚያስተጋባ ጠንካራ መንፈስ እንዳላቸው የሚመሰክርላቸው የሶስት ልጆች እናትና የልጅ ልጅ ማየት የቻሉ እንግሊዞች ቢያገኟቸው ጠንካራዋ እመቤት (The Iron Lady) የሚሉላቸው አይነት ናቸው፡፡
ኢህአዴግ የጸረ ሽብር አዋጁ ማሟሻ በማድረግ እነ ጄነራል ማሞን አጥረግርጎ ሲያስር እማዋይሽም ሚያዚያ 16 / 2001 በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ የሽብር ግብረ ሀይሉ በአዋጁ በሚጠረጥራቸው ሰዎች ላይ መረጃ የመሰብሰብ ልቅ የሆነ ስልጣን የተቀዳጀ ቢሆንም ተጠርጣሪዎቹን ወንጀለኛ ለማድረግ የተጠቀሙት ድብደባንና ማሰቃየትን ነበር፡፡
እማዋይሽ የዚሁ ግፍ ሰለባ በመሆናቸው የሰው ጆሮ ሰምቶ ሊሸከመው የማይችለው አይነት ስቃይ አስተናግደዋል፡፡ወደ መርማሪዎቻቸው ቢሮ አይናቸውን በጨርቅ ተሸፍነው ይገቡ የነበሩት እማዋይሽ ልጆቻቸው በሚሆኑ መርማሪዎች ልባሳቸው ወልቆ እርቃናቸውን ተደብድበዋል፣ ጡቶቻቸው በኤሌክትሪክ ሽቦ ተጠብሷል፣እጆቻቸው ታስሮ ከደረጃ ላይ በጡጫ ተገፍትረው እንዲወድቁ ተደርገዋል፡፡ ይህን ሁሉ ስቃይ ያስተናገዱት ‹‹ከሌሎቹ ታሳሪዎች ጋር መንግስት ለመገልበጥ ከግንቦት 7 ትዕዛዝ ተቀብለን ሞክረናል››ብለሽ ፈርሚ ተብለው ነው፡፡
ስቃዩ ሰው ሊሸከመው የሚችለው አልነበረምና እማዋይሽ አጅ ሰጥተው መርማሪዎቹ የሚሏቸውን አደረጉ፡፡ ፍርድ ቤቱም በዚህ መንገድ የቀረበለትን እንደ ማስረጃ ቆጥሮ እማዋይሽ ላይ የዕድሜ ልክ እስራት ወሰነባቸው፤ እማዋይሽ ያለፉትን ስድስት አመታት በወህኒ ቤት ያሳለፉ ሲሆን በምርመራ ወቅት ጡታቸው ላይ የደረሰው በኤልክትሪክ የተደረገ ማሰቃየት ህመም ፈጥሮባቸው በስቃይ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የተሻለ ምርመራ እንዳያገኙ ከመደረጉም በላይ የታዘዙላቸው መድሀኒቶች ዋጋቸው ከወህኒ ቤቱ አቅም በላይ ነው መባሉ ይነገራል፡፡
እኚህን በዚህ ስርዓት የግፍ ጡጫ ያረፈባቸውን እናት በቃሊቲ ወህኒ ቤት አግኝቼ መጎብኘት በመቻሌ በቅርቡ በተለቀቀው የማዕከላዊ የግፍ ሚስጥር ሪፖርት የተጠቀሰው የጭካኔ ድርጊት እውነት ለመሆኑ እንድመሰክር አድርጎኛል፡፡ ሙሉውን ሪፖርት ለማድመጥ ሊንኩን ይጠቀሙ
ክብር የግፍ በትር እያረፈባቸው ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ይሁን

Comments